ብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት የ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም እና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ከሰራተኞች ጋር ዉይይት ተካሄደ

ሐምሌ 23 ቀን 2018 ዓ.ም : የ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸምና ፣ በቀጣዩ በ2019 በጀት ዓመት ሊተገበሩ የታቀዱ ዋና ዋና ግቦችንና ኦፕሬሽናል ተግባሮች ላይ የኢንስቲትዩቱ ስራ አመራር ከሰራተኛዉ ጋር ዉይይት አካሄደ።
በበጀት ዓመቱ ከተመዘገቡት ስኬቶች መካከል የፋይናንስና የምርት አቅም ዕድገት ይጠቀሳሉ። በበጀት አመቱ 314 ሚሊዮን ዶዝ ክትባት በማቅረብ ካለፈው አመት 25 በመቶ ብልጫ አስመዝግቧል፡፡ ከገቢ አንፃርም ከክትባት፣ ሳላይንና፣መድሐኒት ሽያጭ እንዲሁም ከባዮሎጂካልና ከልዩ ልዩ አገልግሎቶች አጠቃላይ ገቢ የዕቅዱን 99 በመቶ በማሳካት 59 በመቶ ከባለፈው አመት የገቢ ዕድገት ያሳየ ሲሆን፣ ከታክስ በፊት የእቅዱን 126 በመቶ ትርፍ በማግኘት ካለፈው አመት ሲነጻጸር 25.62 በመቶ የትርፍ እድገት በማሳካት ከፍተኛ አፈፃፀም አስመዝግቧል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ታከለ አባይነህ የ2018 በጀት ዓመት አጠቃላይ አፈጻጸም ሪፖርትን ያቀረቡ ሲሆን፣ ተቋሙ ያለፉትን ስኬቶች አስጠብቆ የሚቀጥልበትን አቅጣጫ አመላክተዋል።
በመቀጠልም የዕቅድ ክትትልና ግምገማ ዋና የስራ ክፍል ኃላፊ አቶ ፍቃዱ አበራ የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድን ለተሳታፊዎች በዝርዝር አቅርበዋል።


የኦፕሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር በሬቻ ባይሳ በበኩላቸው በቀጣይ ዓመት ምርትና ምርታማነትን ይበልጥ ማሳደግ በሚቻልባቸው ስልታዊ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ማጠቃለያ ሐሳብ ሰጥተዋል።
በመድረኩ ላይ የተቋሙ ሠራተኞች ተቋማዊ ዕድገትን የሚደግፉ ገንቢ ሐሳቦችንና በበጀት አመቱ ምርትና ምርታማነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳደሩ ችግሮችና የመፍትሔ ሃሳቦች ላይ ትኩረት በማድረግ እንዲሁም ለስራ አመራሩ የተለያዩ ጥያቄዎችን ሰንዝረዋል። ከተነሱት አንኳር ነጥቦች መካከል የተተኪ የሰው ኃይል ዝግጅትን (Succession Planning) ማጠናከር፣ በክትባት ምርት ሂደት ላይ ያጋጠሙ የማሽነሪና የአሰራር ተግዳሮቶችና መፍትሔዎቻቸው፣ እንዲሁም በቀጣይ መሻሻልና ትኩረት ሊሰጣቸው በሚገቡ ተቋማዊ አሠራሮች ዙሪያ ሰፊ ውይይት ተደርጓል።

ለተነሱት ጥያቄዎችና አስተያየቶች በኢንስቲትዩቱ ከፍተኛ አመራሮች አማካኝነት ዝርዝር ምላሽና ማብራሪያ በመስጠት ከሰራተኛው የተነሱ ለተቋሙ ስኬት ገንቢ የሆኑ ሃሳቦችን ስራ አመራሩ እንደ ግብአት ወስዶ ወደፊት ሊሰራባቸው እንደሚገባ በማመን የጋራ ግንዛቤ ወስዷል። በመጨረሻም፣ መላው የኢንስቲትዩቱ ሠራተኞችና አመራሮች የተያዘውን የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ በላቀ ውጤት ለማሳካት በቁርጠኝነት ለመሥራት የጋራ መግባባት ላይ ተደርሶ መድረኩ ተጠናቋል።
