በክትባት ስርጭትና አገልግሎት አስጣጥ የግሉ ዘርፍ ሚና በሚል ከደንበኞች ጋር ዉይይት ተካሄደ

በብሔራዊ የእንሰሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት በክትባት ስርጭትና አገልግሎት የግሉ ዘርፍ ሚና በሚል ከፌደራል ግብርና ሚ/ር እና፣ ከኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎቸ፣ የክልል ግብርና ቢሮ የእንስሳት ጤና ዘርፍ ሃላፊዎች እና በእንስሳት ጤና ላይ ከተሰማሩ ከግል ዘረፉ የተገኙ ተሳታፊዎች፣ በተገኙበት የግማሽ ቀን ዉይይት ተካሄደ፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ታከለ አባይነህ እንደገለጹት የምክክር መድረኩ ዋና አላማ በኢትዮጰያ የእንስሳት ክትባት ስርጭት፣ አገልግሎትና ተደራሽነትን በተመለከተ አሁን ያለውን አሰራር እንዴት ማሻሻል እንደሚቻልና በዚህ ላይ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ የሚኖረውን አስተዋጻኦ ላይ የጋራ ግንዛቤ እንዲኖርና ለቀጣይ ወይይቶችና መፍትሄ እርምጃዎች መነሻ ሃሳብ ለማቅረብ ነው፡፡ በመቀጠልም የክትባት ተደራሽነት ማለት የእንስሳት ክትባት በእያንዳንዱ የሀገሪቱ ኮርነር ወይም አርብቶ አደር በተፈለገው መጠንና ጊዜ ማግኘት መቻል እንደሆነ በመግለጽ፣ ከዚህ አንጻር ሲታይ ያለው ነባራዊ ሁኔታ የሚያሳየው የክትባት ተደራሽነት ላይ ውስንነት እንዳለ አስረድተዋል፡፡

የኢንስቲትዩቱ የግብይትና ሽያጭ ዳይሬክተር አቶ መስፍን ታደሰ የኢንስቲትዩቱን የ2017 በጀት ዓመት የክትባት ስርጭትና ሽያጭ አፈጻጸም እንዲሁም የ2018 በጀት ዓመት የክትባት አቅርቦት ዕቅድ ፣ በክትባት ስርጭትና አገልግሎት ዙሪያ ያሉትን ተግዳሮቶችንና የሚሻሻልበትን እድሎችና አቅጣጫዎች በመጠቆም ገለጻ አድርገዋል፡፡

ከግሉ ዘርፍ በእንስሳት ጤና ላይ የተሰማሩት የSmart Livestock Solutions (SLS) ባለቤት ዶ/ር ብርሃኑ አድማሱ የግሉ ዘርፍ በእንሰሳት ክትባት ስርጭትና አገልግሎት አሰጣጥ ፍራንቻይዝ ሞዴል በቦረና ዞን የተከናወነውን ተሞክሮ የሙከራ ጥናት (pilot study) አቅርበዋል፡፡ ጥናቱ በካናዳው IDRC የፋይናንስ ድጋፍ ተፍትስ ዩንቨርሲቲ፣ አቢሲኒያ አግሮቬት፣ የብሔራዊ የእንሰሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት የተሳተፉበት ሲሆን ከፍተኛ ዋጋ ያለውን የፍየል ሳንባ በሽታ ክትባትን እንደ ሞዴል በመጠቀም የተከናወነ ሲሆን የጥናቱ ውጤት እንደሚያሳየው ተጠቃሚው ክትባት በሚፈልገው መጠንና ጊዜ እስከቀረበለት ድረስ የክትባቱንና የአገልግሎት ዋጋን ጨምሮ ለመክፈል ፈቃደኛነቱን ያሳየበትና የተሰጠው የክትባት አገልግሎቱም በሽታን ከመከላከል አንጻር ተመዝኖ ውጤታማ ና የተሻለ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን የእንስሣት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሃሚድ ጀማል እንደገለጹት የውይይቱ አጀንዳ በጣም አስፈላጊና የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ የእንስሳት ጤና አገልግሎት ላይ መሻሻል እንደሚያመጣ የሚታመንበትና ሊሰራበት እንደሚገባ ጠቁመው፣ነገር ግን ከሚያስፈልግው የሎጂስቲክና የቁጥጥር ስርአት አንጻር ዝግጅትና ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚፈልግ መሆኑን አሳውቀዋል፡፡ ከዚህ አንጻር አጀንዳው በኢንስቲትዩቱና በሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ውሳኔ ሰጪ አካላት የሚሳተፉበት ከፍተኛ መድረክ መቅረብ እንዳለበት አሳስበው፣የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣንም የቀረበውን ሃሳብ እንደሚደግፍና የበኩሉን አስተዋጽኦና ዝግጅት እንደሚያደርግ አሳውቀዋል፡፡
በውይይቱ አሁን ያለው የእንስሳት ክትባት ስርጭትና አገልግሎት አሰጣጥ በመንግስት ብቻ እየተሰራ እንደሆነና ይህ ደግሞ መንግስት ካለበት የተለያዩ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ሃላፊነቶች አንጻርና ክትባትን የቅዝቃዜ ሰንሰለቱን ጠብቆ ለተጠቃሚው ለማድረስ የሚጠይቀው በጀት፣ጊዜና ሎጂስቲክ ቀላል ስላልሆነ የክትባት ተደራሽነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳሳደረ ከግንዛቤ ተወስዷል፡፡
ለዚህ አማራጭ መፍትሄ የግሉን ዘርፍ ማሳተፍና ወይም ወደ ዘመናዊ የእንስሳት አረባብ ዘዴ መሸጋገር (transformation to intensive commercial farming) ስለሚጠይቅ፣ ከዚህ አንጻር፣የሀገሪቱ ህግ ማእቀፍ፣ አገልግሎቱን እየሰጠ ያለው የግብርና ሚ/ር ዝግጁነት፣ የክትባት ስርጭትና አገልግሎት ቁጥጥር ስርአትን ማጠናከር፣ የግሉ ዘርፍና የተጠቃሚው አመለካከትና ዝግጁነት፣ እንዲሁም የክትባት ምርትና አቅርቦት ላይ ዝግጁነት ውሳኝ መሆኑ በውይይቱ ተጠቁሟል፡፡
በመድረኩ ከተሳታፊዎች በክትባት ስርጭት፣ተደራሽነት አያያዝና አጠቃቀም ዙሪያ ያሉ ተግዳሮቶችን እና በተለይም የኢንስቲትዩቱ የቀጣይ ዕቅድ እና በዘርፉ መሻሻል ስለሚገባቸዉ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ በተሳታፊዎች ለተነሱ የተለያዩ ሃሳቦች ተነስተው ማብራሪያ ተሰጥተል፡፡ የኢንስቲትዩቱ የኦፕሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር በሬቻ ባይሳ እንዳነሱት፣ በዚህ በጀት አመት የተፈጠረውን የአፍ ተግር በሽታ ክትባት እጥረት እንደ ምሳሌ በማንሳት፣ በደንበኛ ፍላጎት የእንስሳት ክትባትን ለማቅረብ፣ እያንዳንዱን ክትባት ለማምረት የራሱ ጊዜ የሚፈልግ በመሆኑ ደንበኞች በቅድሚያ በቂ ጊዜ በመስጠት ፍላጎታቸውን ማሳውቅ እንደሚገባቸው ጠቁመዋል፡፡ አያይዘውም ክትባትን በሽታ ፍንዳታን ጠብቆ መስጠት ሳይሆን ወቅቱን ጠብቆ ማስከተብ እንደሚገባና በሽታ ፍንዳታ ከተከሰተ በሃላ የሚሰጥ ክትባት እምበዛም ጥቅም እንደሌለው ግንዛቤ ስጥተዋል፡፡
በመጨረሻም የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አሁን ያለውን የዘመናዊ እንስሳት እርባታ እድገትና በተለይም በዶሮ እርባታ የሚታየውን ፈጣን እድገት፣ እየተተገበረ ያለውን የሌማት ትሩፋት ፕሮግራም እንዲሁም የክትባት ተደራሽነት እንደሚሻሻል ታሳቢ በማድረግ የክትባት አቅርቦትን ለማሳደግ ኢንስቲትዩቱ የክትባት ማምረቻ የማስፋፊያ ፕሮጀክት የአዋጪነት ጥናት በሂደት ላይ እንዳለና ጥምር ክትባቶችን ለማምረት የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር እያከናወን መሆኑን በመጥቀስ፡ ማጠቃለያ ተሰጥቶ ዉይይቱ ተጠናቋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ኮሙኒኬሽን
ሰኔ 26 ቀን 2017 ዓ.ም
