ብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት የ2018 በጀት ዓመት ሀገራዊ የልማት ዕቅድ ፣ የኢንስቲትዩቱን የ2017 በጀት አመት የስራ አፈፃፀም እና የቀጣይ አምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ የተቋሙ ስራ አመራር ከሠራተኞች ጋር ዉይይት አደረጉ
በዉይይቱ የ2018 በጀት ዓመት ሀገራዊ የልማት ዕቅድን ያቀረቡት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ታከለ አባይነህ ሲሆኑ አለምአቀፍ የኢኮኖሚ አዝማሚያ፣የማክሮኢኮኖሚ ዕቅድ፣የፋይናንስ ዘርፍ፣የግብርናና አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ዕቅድ በተለይም ከኢንስቲትዩቱ ተልዕኮ አንጻር ተያያዥ የሆኑ እንደ የሌማት ትሩፋት ያሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ ከኢንስቲትዩቱ የሚጠበቁ ስራዎችን በተመለከተ ለዉይይት አቅርበዋል፡፡ ሀገራዊ ጥቅምን የሚያጠናክሩ ማዕቀፎችን ማስፋት፣በሁሉም ዘርፍ ቴክኖሎጂና በዕዉቀት ሽግግር ህዝብን በማሳትፍ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ከዕቅዱ የቀጣይ የትኩረት መስክ መሆኑን መገንዘብ ተችሏል፡፡

የኢንስቲትዩቱ የ2017 በጀት ዓመት የኦፕሬሽናልና የፋይናንስ አፈፃፀም እንዲሁም ከ2018 -2022 የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ በፕላንና ፕሮግራም አገልግሎት ሃላፊ በአቶ ፍቃዱ አበራ ቀርቧል፡፡ ያለፉት አምስት ዓመታት አለም አቀፍ የክትባት ገበያዉ ገፅታ እና የኢንስቲትዩቱ ድርሻ እንዲሁም ኢንስቲትዩቱ በክትባት አቅርቦት ያለፉት አምስት አመታት ከ2013 እስከ 2017 ንጽጽር ሲታይ በ2013 267.85 ሚሊዮን ዶዝ በማቅረብ፣በ2016 በጀት ዓመት 288.20 ሚሊዮን ዶዝ ክትባት በማቅረብ የአምስት አመቱ ከፍተኛ አፈጻጸም እንደነበር ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡ የምርምርና ስርፀት ስራዎች በታቀደዉ መሰረት እየተከናወነ እንደሚገኝና የእንስሳት ክትባት እና መድሃኒት ምርት መጠንን ማሳደግ፣የደንበኞች ፍላጎትን መሰረት በማድረግ አዳዲስ የምርት አይነቶችን መጨመርና የምርት አቅርቦት ተደራሽነትን ማስፋት የስትራቴጂክ ዕቅዱ የትኩረት መስክ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በዘርፉ የገበያ ተወዳዳሪነትን ለማስቀጠል በራስ አቅምና በዘርፉ ከተሰማሩ የዉጪ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ጥምር የማምረት አቅምን በማጎልበት በተለይም የዶሮ ክትባትን በደንበኞች ፍላጎት መሰረት ለማቅረብ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ታከለ አባይነህ ጠቁመዋል፡፡አመታዊና ስትራቴጂክ እቅዱን ለማሳካት፣ምርትና ምርታማነት ላይ እንቅፋት የሆኑ ችግሮችን በመፍታት በእንሰሳት መድሃኒት ምርት ይበልጥ ተደራሽ ለመሆንና የኢንስቲትዩቱን ገቢ በማሳደግ ትርፋማነትን ለማስቀጠል ይሰራል ብለዋል፤ ተጨማሪ ገቢ ሊያስገኙ የሚችሉ የተለያዩ ባዮሎጂካልስና የመመርመሪያ ኪቶችንም በተሻለ መልኩ ለማቅረብ የምርምር ማልማት ስራ ላይ በትኩረት ለመስራትና ለዚህም አመቺ የሆነ የምርምር አደረጃጀት ለማድረግ እንደታቀደ አሳውቀዋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ የኦፕሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር በሬቻ ባይሳ እንደገለፁት አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በክትባትና መድሐኒት ገበያ ላይ ከፍተኛ ውድድር እየታየ በመሆኑና ወደፊት ኢንስቲትዩቱ የገበያ ተወዳዳሪነቱን ለማስቀጠል ለማሽኖች ቅድመ ጥገና በማድረግ ምርት ላይ የሚፈጥረዉን ተጽዕኖ በመቀነስ በተለይም የሰው ኃይል በስራ ላይ ያለውን ውጤታማነት በማሻሻል በቀጣይ የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በተለያዩ የኢንስቲትዩቱ የስራ እንቅስቃሴዎች ላይ ከሰራተኞች ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች በአመራሩ ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን በአጠቃላይ ሠራተኛውና ስራ አመራሩ በ2017 በጀት ዓመት አፈፃፀም ላይ ያጋጠሙ የዉስጥና ዉጫዊ ችግሮች ላይ ዉይይት በማድረግ ቀጣይ የኢንስቲትዩቱን አፈፃፀም የተሻለ ለማድረግና ለስኬት ሁሉም የበኩሉን እንደሚወጣ የጋራ ግንዛቤ ላይ ተደርሷል፡፡
በሠራተኛው በኩል ከነባራዊ የኑሮ ውድነት ጋር ተያይዞ ለተነሱ ጥያቄዎች የኢንስቲትዩቱ ስራ አመራር ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ከሚመለከተው የተቋሙ የበላይ አመራር ጋር እየተሰራ እንደሆነና የመዋቅር ጥናት ያለበትን ደረጃ ለሰራተኛዉ ተገልጿል፡፡

ለዘገባው፡- የኢንስቲትዩቱ ህ.ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን
ሐምሌ 2017 ዓ.ም
