ለወተት ከብት አርቢዎች የፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒት መቋቋም (AMR) መከላከያ ስልጠና ተሰጠ


በወተት ከብት እርባታ ላይ በሽታን ለመከላከል፣ የወተትን ደህንነት ለመጠበቅ እና የአንቲማይክሮቢያል መድኃኒቶችን በኃላፊነት ለመጠቀም የሚያስችል የአንድ ቀን የስልጠና መርሃ ግብር ተካሄደ። ይህ ስልጠና በተለይ ለቢሾፍቱ የወተት ከብት አርቢዎች የአንቲማይክሮቢያል መድኃኒት መቋቋም (AMR) በ “አንድ ጤና” (One Health) የተቃኘ በቁጥጥር እና አማራጭ መፍትሄዎች ላይ ያተኮረ ነው።
በብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት (NVI) አመራሮችና ከፍተኛ ባለሙያዎች የተመራው ይህ ስልጠና በበርካታ ዋና ዋና ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊ ግንዛቤ አስጨብጧል::
የኢንስቲትዩቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ታከለ አባይነህ በመክፈቻ ንግግራቸዉ የፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒቶች መላመድ የእንስሳትን ጤና ብቻ የሚመለከት ችግር እንዳልሆነና ከእንስሳት ወደ ሰው፣ ከሰው ወደ እንስሳ እና በአካባቢ ውስጥ በተለያዩ መንገዶች ሊሰራጭ የሚችል የወቅቱ ችግር በመሆኑ የሰው ጤና፣ የእንስሳት ጤና እና የአካባቢ ጤና በአንድነት የሚታዩበትን “አንድ ጤና” (One Health) አቀራረብ መከተል አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸዉ AMR በወተት ከብት እርባታ ላይ ያለውን ተፅዕኖ፣ መንስኤዎቹንና ስርጭቱን በስፋት አብራርተዋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ተመራማሪ ዶ/ር ንጉሱ ብርሃኑ፤ በከብቶች ጤና ችግሮች፣ ባዮሴኩሪቲ (Biosecurity) እና በበሽታ መከላከል ዙሪያ ስልጠና ሰጥተዋል። ንጹህ ወተት የማለብ ስርዓት ፣ የመኖሪያ አያያዝ፣ የመኖና የውሃ ንጽህና እንዲሁም ክትባትን በመጠቀም የAMR ስርጭትን እንዴት መቆጣጠር እንደሚቻል በኢንስቲትዩቱ የባክቴሪዮሎጂ ጥናት መሪ ተመራማሪ ዶ/ር አረጊቱ መኩሪያው አማካኝነት ሰፊ ትንተና ቀርቧል። አርቢዎች ኃላፊነት ያለው የመድሃኒቶች አጠቃቀም እና አደገኛ አጠቃቀሞችን እንዲያስወግዱ የሚያስችለውን የ “STOP–CHECK–ACT” መርህ እና የእርባታ AMR የተግባር ዕቅድ በኢንስቲትዩቱ የምርምርና ስርጸት ዋና የስራ ክፍል ሃላፊ ዶ/ር ምርትነህ አካሉ አማካኝነት ቀርቧል።

በተጨማሪም የአንቲባዮቲክ መድኃኒቶችን አጠቃቀም ለመቀነስና የፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒት መቋቋምን (AMR) ለመከላከል በብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት (NVI) በአለም አቀፍ የልማት ምርምር ማዕከል (IDRC) ድጋፍ እየተካሄደ ስላለው፣ በናኖቴክኖሎጂ ላይ የተመሠረተ አማራጭ የሕክምና መፍትሄ የማበልጸግ የምርምር ፕሮጀክት ማብራሪያ ሰጥተዋል። በፕሮጀክቱ ከተገኙ ዋና ዋና ውጤቶች መካከል በናኖፓርቲክል ቴክኖሎጂ የተዘጋጁ አማራጭ የሕክምና ንጥረ ነገሮችን ማበልጸግ፣ በጥጃዎች ላይ የተካሄዱ የሙከራ ጥናቶች አበረታች ውጤት ማሳየታቸውና በተለይም QSI-5 የተባለው የሕክምና አማራጭ በበሽታ አምጪ ባክቴሪያዎች ስርጭት ላይ የመቀነስ አቅም ማሳየቱ ተጠቃሽ ናቸው። በተጨማሪም GI-7a የተባለ ሌላ አማራጭ የሕክምና ንጥረ ነገር ተዘጋጅቶ የሙከራ ሥራዎች እየተካሄዱ መሆኑን ገልጸው፣ የምርምር ውጤቶቹ ወደፊት በእንስሳት ሕክምና የአንቲባዮቲክ ጥገኝነትን ለመቀነስ ጠቃሚ አማራጭ ሊሆኑ እንደሚችሉ አብራርተዋል።
የግብይትና ሽያጭ ዋና የስራ ክፍል ሃላፊ አቶ መስፍን ታደሰ የNVI የእንስሳት በሽታ መከላከያ ክትባቶችና የመድኃኒት ምርቶችን አጠቃቀምና አተገባበር ያብራሩ ሲሆን፣ በመርሃ ግብሩ ማጠናቀቂያ ላይ በተሳታፊዎች መካከል የልምድ ልውውጥና ውይይት ተካሂዶ ስልጠናዉ ተጠናቋል::

