የብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት 60ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ተከበረ ።
ብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት በእንስሳት ኃብት ምርታማነትን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የሚያበረክተውን አስተዋጽዖ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ።
ብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት 60ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች አክብሯል።
በዓሉም ተቋሙ ቅጥር ግቢ በቢሾፍቱ ከተማ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የዘርፉ ተመራማሪዎችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ተከብሯል። በበዓሉ በኢንስቲትዩቱ 60 ዓመታት የጉዞ ስኬቶች የሚያሳዩ ሥራዎች በኤግዚቢሽን ለዕይታ የቀረቡ ሲሆን የአርብቶና አርሶ አደሩን ግንዛቤ የሚያሳድግ የተቋሙን የ60 ዓመታት ስኬት ጉዞ አውደ-ርዕይ ለዕይታ ቀርቧል።
በበዓሉ አከባበር ላይ የተገኙት የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር)እንደገለጹት፤ ኢንስቲትዩቱ በአገሪቱ እንስሳት ኃብት ላይ ሊደርስ ይችል የነበረውን ጉዳት በመከላከል ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽዖ አበርክቷል። በዚህም ክትባት በማምረትና በመስጠት በሽታን ቀድሞ ለመከላከል የራሱን ድርሻ መወጣቱን ጠቁመው፤ ኢንስቲትዩቱ ራሱን በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች በማጎልበት የበለጠ መሥራት እንዳለበት ተናግረዋል። ለዚህም ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ታከለ አባይነህ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢንስቲትዩቱ በሰው ኃይልና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት ከኢትዮጵያ አልፎ ለተለያዩ አገራት በሚልከው የእንስሳት ክትባት የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት የአገሪቱን ኢኮኖሚ እየደገፈ ነው። በምርምርና በእንስሳት ጤና ክትባት ላይ ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም ጠቅሰዋል። በዚህም የኢትዮጵያን የእንስሳት ኃብት ጤንነት ከመጠበቅ ባለፈ ከአራት ዓይነት ወደ 23 የክትባት መድኃኒት ምርት ዓይነቶች ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።
በዓመት 4 ሚሊየን የክትባት መድኃኒት የማምረት አቅሙንም ወደ 300 ሚሊየን በማሳደግ የአገር ውስጥ የእንስሳት ክትባት ፍላጎትን ሙሉ በሙሉ መሸፈን መቻሉን ገልፀዋል። የክትባት ምርቱን ለሀገር ውስጥ ገበያ ከማቅረብ ባለፈ ለ33 የውጭ አገራት በመላክ የውጭ ምንዛሬን ማስገኘቱን አብራርተዋል። በቀጣይም የአገርና የውጭ የክትባት ፍላጎት መሠረት በማድረግ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የእንስሳት ክትባት ማምረቻ ላቦራቶሪ ኮምፕሌክስ ለመገንባት ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ኃብታሙ ኃይለሚካኤል፤ ኢንስቲትዩቱ የእንስሳት ኃብት ጤንነት በመጠበቅ ለሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ የማይተካ ሚና እየተወጣ ነው ብለዋል። ዓለም አቀፍ የእንስሳት ክትባትና መድኃኒት ጥራትና ተወዳዳሪነትን በማሳደግ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ እያቀረበ የሚገኘውን የማምረት አቅም ለማሳደግ የባለድርሻ አካላት ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።
በኢንስቲትዩቱ የግብይት ዳይሬክተር መስፍን ታደሠ በበኩላቸው፤ ከአገር ውስጥ አልፎ ባለፉት 11 ወራት ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማስገኘቱን ገልፀዋል። ብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት በ1956 ዓ.ም በኢትዮጵያና በአፍሪካ “ደስታ” የተሰኘ የእንስሳት በሽታ መከሰቱን ተከትሎ የተመሠረተ የምርምር ተቋም መሆኑ ይታወቃል።
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 22/2016(ኢዜአ)