የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታዎችና አስተዳደር የስራ አመራር አባላት በብሔራዊ የእንሰሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት የስራ ጉብኝት አደረጉ

ኢንስቲትዩቱ የእንሰሳት ሀብት ዘርፉን ለመደገፍ ለእንሰሳት ጤና ጥበቃ የሚያገለግሉ ግብአቶችን እንዲያመርት በተሰጠዉ ተልዕኮ መሰረት በምርምር የተደገፉ 23 አይነት የእንሰሳት በሽታ መከላከያ ክትባቶችን ፣ የእንሰሳት በሽታ መመርመሪያ የሚያገለግሉ ባዮሎጂካሎችን እንዲሁም በ2013 ዓ.ም የእንሰሳት መድሃኒት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ተመርቆ 12 አይነት የእንሰሳት መድሃኒት ለማምረት ታቅዶ  ወደ ምርት መገባቱን የገለጹት በዕለቱ ስለ ተቋሙ መግለጫ ያቀረቡት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ታከለ አባይነህ ናቸዉ፡፡

የኤሌክትሪክ ሃይል እጥረትና መቆራረጥ እንዲሁም ግብአቶችንና መለዋወጫ እቃዎችን በወቅቱ ገዝቶ ለማቅረብ የዉጭ ምንዛሬ እጥረት ለተቋሙ ዋና ዋና ተግዳሮቶች እንደሆኑበትና ከመንግስት  የልማት ድርጅቶች ይዞታዎች አስተዳደር ከሚፈልጋቸዉ ድጋፍ መካከል ዘመናዊ የክትባት አመራረት ቴክኖሎጂን ለመተግበርና አዲስ ፕሮቶታይፕ ምርቶቹን በምርምር አበልጽጎ ወደ ምርት ለማስገባት ለሚታቀዱ የምርምር ፕሮጀክቶች የፋይናንስ ድጋፍ ተጠቃሽ መሆናቸዉን ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡

በጉብኝቱ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታዎች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሐብታሙ ሀ/ሚካኤል፣የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ትዕግስቱ አምሳሉ፣የስርዓት ግንባታ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ይርጋ እና የተቋሙ ሥራ አመራር አባላት የተገኙ ሲሆን በአጠቃላይ ኢንስቲትዩቱ የሚያከናዉናቸዉን ተግባራትና ልዩ ልዩ ላቦራቶሪዎችን በጎበኙበት ወቅት ለተነሱ ጥያቄዎች ባለሙያዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታዎች አስተዳደር ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ኢንስቲትዩቱ ያለበትን ችግር ለመፍታት የበኩላቸዉን ድጋፍ እንደሚያደርጉ በጉብኝቱ ወቅት አረጋግጠዋል፡፡

መጋቢት 20 ቀን 2014 ዓ.ም

የኢንስቲትዩቱ ህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን