በብሔራዊ የእንሰሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት ከዶሮ አርቢ ደንበኞች ጋር ዉይይት ተካሄደ


መጋቢት 16 ቀን 2017 ዓ.ም፡- የዉይይቱ ዋና ዓላማ ኢንስቲትዩቱ በዋናነት ከሚያመርታቸዉ
የክትባት ምርቶች በተጨማሪ ለማንኛዉም ዶሮ አርቢ የእንቁላል ጣይ ዶሮ ጫጩት ለማቅረብ
በዝግጅት ላይ እንደሆነ ለደንበኞች ይፋ ለማድረግ ነዉ፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ታከለ አባይነህ ኢንስቲትዩቱ ጥምር ክትባቶችን በምርምር
ለማበልፀግ እየሰራ እንደሆነና ለአጭር ጊዜ መፍትሔ በ joint Venture ከዉጭ ክትባት
አምራች ድርጅቶች ጋር በመተባበር ጥምር የዶሮ ክትባቶችን ለማቅረብ በሂደት ላይ እንደሆነ
ገልጸዉ የዉይይቱ አስፈላጊነት የእነዚህንም ክትባቶች የደንበኞችን ፍላጎት ለማወቅ እንደሆነ
እና በተጨማሪም ከዶሮ አርቢዎች ተቀራርቦ ለመስራት የሚያስችል ሁኔታ በመፍጠር የራስን
አቅም ገንብቶ ክትባት በዓይነትም ሆነ በጥራት በማሳደግ ገበያ ዉስጥ ይበልጥ ተወዳዳሪ
በመሆን የራሳችንን ሚና ለመወጣት ጥረት እያደረግን ነዉ ብለዋል፡፡
በመድረኩ የግብይትና ሽያጭ ዳይሬክተር አቶ መስፍን ታደሰ የኢንስቲትዩቱን የዶሮ ክትባት
አቅርቦት እና አለምአቀፍ ገበያዉን፣የምርምርና ስርጸት ዳይሬክተር ዶ/ር ምርትነህ አካሉ በዶሮ
እርባታ ዘርፍ በሽታን ከመከላከል አንጻር ያሉ ተግዳሮቶችንና እየተከናወኑ ያሉ የምርምር
ስራዎችን እንዲሁም የሽያጭ እና ደንበኞች አገልግሎት የቡድን መሪ አቶ ደበበ ሽመክት የዶሮ
አያያዝን በተመለከተ አርቢዎች ሊያደርጉ የሚገባቸዉን ጥንቃቄ እንዲሁም በተቋሙ
እየተመረተ ለገበያ ስለቀረበዉ የዘር እንቁላል እና በቀጣይ ለገበያ ስለሚቀርበዉ የእንቁላል ጣይ
ዶሮ ጫጩት ዝርያ ሙያዊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ደንበኞችም ኢንስቲትዩቱ 60 ዓመት ልምድ ያለዉ ተቋም እንደመሆኑ ከክትባት ምርት ባሻገር
ሌሎች ተያያዥ ምርቶችን በማምረት ዘርፉን ከዚህ በበለጠ ማገዝና የተሻለ ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ
ሞዴል ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ኮሙኒኬሽን
ለዘገባዉ፡- አደይአበባ ታምሩ