የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ እና የመንግስት ልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ኢንስቲትዩቱን ጎበኙ
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚደንት ክቡር ዶ/ር ዮሐንስ አያሌው እና፣ የመንግስት ልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ትግስቱ አምሳሉ እንዲሁም የባንኩ አስተዳደር እና የሚመለከታቸው የስራ ሃላፊዎች የብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩትን የተለያዩ የክትባት ማምረቻ ላብራቶሪዎች፣የእንሰሳት መድሃኒት ማቀነባበሪያ ፋብሪካዉንና የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ያሉበትን የስራ እንቅስቃሴ ጎበኙ፡፡
የኢንስቲትዩቱ የኦፕሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር በሬቻ ባይሳ ፣የክትባት ማምረቻ ላብራቶሪዎች ያሉበትን ደረጃና የማምረት አቅም፣የመድሃኒት ማቀነባበሪያ ፋብሪካዉን እንቅስቃሴና የኢንስቲትዩቱን የምርምር ስራዎችን ገለጻ ያቀረቡ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ኢንስቲትዩቱ የአገር ውስጥ የእንስሳት ክትባት ፍላጎትን ሙሉ ለሙሉ በመሸፈን ለክትባት ግዥ ይወጣ የነበረን የውጭ ምንዛሪ በማስቀረት ከፍተኛ አገራዊ አስተዋፅኦ እደረገ መሆኑን አሳውቀዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ በአሁኑ ጊዜ 23 ዓይነት የእንስሳት በሽታ መከላከያ ክትባቶችን እያመረተ ሲሆን፣የሚያመርታቸውን ክትባቶች ወደ ተለያዩ የአፍሪካ አገራት በመላክ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ማግኘት መቻሉን፤እንዲሁም ተቋሙ ሲመሰረት የተገነቡ ላብራቶሪዎችን ዘመናዊ የአመራረት ዘዴ /GMP በሚያሟላ ላቦራቶሪ ኮምፕሌክስ የመቀየር፣የእንስሳት በሽታ መመርመሪያ ኪት ለማምረት እና በመርፌ የሚሰጡ መድሃኒቶችን ማምረት የሚያስችል ላቦራቶሪ ለመገንባት በእቅድ ላይ እንደሆነና እነዚህን ወደ ተግባር ለመለወጥ የታሰቡ ፕሮጀክቶችን የሚመለከታቸዉ የመንግስት አካላት ሊደግፉት እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የመንግስት ልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር የማኑፋክቸሪንግና ህትመት ዳይሬክተር አቶ ገረመው ቀኖ ኢንስቲትዩቱ በቅርቡ ለአፍሪካ አህጉር የደስታ በሽታ መጠባበቂያ ክትባት እንዲያመርት በአለም ምግብና እርሻ ድርጅትና በአለም የእንስሳት ጤና ድርጅት መመረጡ ተቋሙ ለሀገር ብቻ ሳይሆን ለአፍካም ከፍተኛ ሚና ያለው መሆኑን በመግለፅ አለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን ለማጎልበትና የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን ያቀዳቸውን ፕሮጀክቶች መደገፍ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ክቡር ዶ/ር ዮሃንስ አያሌዉ ልማት ባንኩ ቅድሚያ ከሚሰጠዉ አንዱ የእንሰሳት ዘርፍ እንደመሆኑ ለተያዙት ፕሮጀክቶች ኢንስቲትዩቱ በሚያቀርበው የአዋጭነት ጥናት /feasibility study ተገምግሞ ፕሮጀክቶቹን ፋይናንስ እንደሚያደረግ አሳውቀዋል፡፡
የመንግስት ልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ትዕግስቱ አምሳሉ በበኩላቸዉ የእንሰሳት ዘርፍ የመንግስት ዋነኛ ትኩረት ሲሆን ኢንስቲትዩቱ ለሃገር ከፍተኛ አስተዋጾ እያበረከተ ያለ ተቋም እንደመሆኑ፤ የደስታ በሽታን ለማጥፋት ያደረገዉ ጥረት እና በሰዉ ሃይልም ትልቅ አቅም ያለዉ እንደመሆኑ የፋይናንስ ችግሩን በመቅረፍ ከታሰቡት ፕሮጀክቶች በተጨማሪም ቢዝነሱን ለማስፋት ሌሎች ፍላጎቶችንም መፍጠር ይቻላል ብለዋል፡፡
በመጨረሻም የብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬከተር ዶ/ር ታከለ አባይነህ ኢንስቲትዩቱ በእንስሳት ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ድጋፍ የሚያደርግ ቁልፍ ተቋም እንደመሆኑ የኢንሰቲትዩቱን የማምረትና የገበያ ተወዳዳሪነት አቅም ለመገንባት የታሰቡ ፕሮጀክቶቹን ተግባራዊ ለማድረግ ኢንስቲትዩቱ ሙሉ አቅሙን በመጠቀም የአዋጭነት ጥናት አከናውኖ ለኢትዮጵያ ልማት ባንክ እንደሚያቀርብ አሳውቀዋል፡፡
የብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት ከተመሰረተ 60 ዓመት ያስቆጠረ ሲሆን፤አሁን ላይ በዓመት 350 ሚሊዮን ዶዝ ክትባት እያመረተ ይገኛል፡፡
ዘጋቢ፡- የኢንስቲትዩቱ የኮሙኒኬሽን ባለሙያ
መጋቢት 21/2016