ክቡር አምባሳደር ድሪባ ኩማ፣ የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር እና የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የስራ ሃላፊዎች ኢንስቲትዩቱን ጎበኙ
የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክቡር አምባሳደር ድሪባ ኩማ እና ሌሎች የባለስልጣን መስሪያቤቱ የስራ ሃላፊዎች በብሔራዊ የእንሰሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት ጳጉሜ 4 ቀን 2014 ዓ.ም የስራ ጉብኝት አደረጉ፡፡
የብሔራዊ የእንሰሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት በምርምር የተደገፉ የተለያዩ የእንሰሳት ክትባቶችንና መድሃኒት የሚያመርት በአመት ወደ 450 ሚሊዮን ዶዝ የእንስሳት ክትባት የማምረት አቅም ያለዉና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የእንስሳት መድሐኒት በማምረት ላይ ያለ ብቸኛ ሀገራዊ ተቋም መሆኑንና ትልቅ ሀገራዊ ፋይዳ ያለው ተቋም መሆኑን የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ታከለ አባይነህ ስለተቋሙ ማብራሪያ ሲሰጡ ገልጸዋል፡፡
በኢንስቲትዩቱ ያለው የመልካም አመራረት ዘዴ፣የዶሮ ክትባት ምርት ላይ ያለዉ አቅምና የወደፊት ዘግጅት፣የክትባትና መድሐኒት ምዝገባን፣የገበያ ድርሻን በተለይም የውጭ ገበያን ከማሳደግና ኢንስቲትዩቱን ማስተዋወቅን በተመለከተ እና ሌሎች ሃሳቦች ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የስራ ሃላፊዎች የተነሳ ሲሆን፤ ከሚመለከታቸዉ የኢንስቲትዩቱ የስራ ሃላፊዎች አስተያየትና ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ክቡር አምባሳደር ድሪባ ኩማ በበኩላቸዉ ሁለቱም ተቋማት አንድን ሀገር ለመገንባት የሚሰሩ እንደመሆናቸዉ ባለስልጣን መስሪያቤቱ የኢንስቲትዩቱ ምርቶች ጥራታቸውን የጠበቁና አለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ባለስልጣኑ እገዛ እንደሚያደርግ ገልፀዋል፡፡
የባስልጣን መስሪያ ቤቱ የእንስሳት ቁጥጥር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ሐሚድ ጀማል በበኩላቸው መስሪያ ቤታቸው የኢንስቲትዩቱ ምርቶችን ጥራታቸውንና ጠብቀው ለተጠቃሚው መድረሳቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን ጠቅሰው፣ይህን አላማ ለማሳካት ከኢንስቲትዩቱ በቅርበት እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡
በሀገር ዉስጥ አቅም የሚመረቱ የእንስሳት ክትባቶች ባለበት ሁኔታ እንደ ሀገር ውስን በሆነ የውጭ ምንዛሪ ከውጭ የሚገቡ ክትባቶች ላይ ቁጥጥር ሊደረግ አንደሚገባም የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ታከለ አባይነህ በማጠቃለያ ንግግራቸዉ ገልጸዋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን
ጳጉሜ 4 ቀን 2014 ዓ.ም