በመንግስት ልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር የኢንስቲትዩቱ የዘጠኝ ወር ዕቅድ አፈጻጸም ተገመገመ

 

ግንቦት 6 ቀን 2016 ዓ.ም – የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር የብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩትን የ2016 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወር ዕቅድ አፈጻጸም ከአስተዳደሩ እና ከኢንስቲትዩቱ የስራ ሃላፊዎች ጋር ገመገመ፡፡

ኢንስቲትዩቱ አፈጻጸሙን ለህዝብ ማሳወቁ ፣የሂሳብ ምርመራን ወቅታዊ ማድረጉ፣የተቋሙ ካፒታል ማደጉ፣ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ለመስራት ያከናወናቸው ተግባራት እና ከታቀዱ ፕሮጀክቶች መጠናቀቅ ጋር የተገናኙ አፈጻጸሞች አበረታች መሆናቸው ታይቷል፡፡

ኢንስቲትዩቱ በዘጠኝ ወሩ የብር 275 ሚሊዮን ሽያጭ ገቢ በማግኘት የብር 118 ሚሊዮን ትርፍ ከግብር በፊት አሳክቷል፡፡ ይህ አፈጻጸሙ ካለፈው ተመሳሳይ በጀት ዓመት አንጻር ሲታይ 33 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ታከለ አባይነህ በሪፖርቱ አመላክተዋል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን በተመለከተም 830 ሺህ የአሜሪካን ዶላር የተገኘ ሲሆን፣ ካለው ተሰብሳቢ ሂሳብ ደግሞ ብር 51.5 ሚሊዮን መሰብሰብ ተችሏል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ጥምር የክትባት ምርት ለማምረትና አዳዲስ ክትባቶችን በማበልጸግ የምርምር ስራዉ በተጠናከረ መልኩ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ኃይለሚካኤል እንደገለጹት በአፈጻጸሙ የታዩ ጠንካራ ጎኖች ሊቀጥሉ እንደሚገባና ተቋሙ ለሀገር ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚሰጥ ስትራቴጂክ ተቋም እንደመሆኑ በሀገር ደረጃ እየተከናወኑ ካሉ  እንደ የሌማት ትሩፋት ፕሮጀክቶች የእንሰሳት ጤናን ከመጠበቅ አንጻር ኢንስቲትዩቱ ትልቅ አስተዋጽኦ ያለዉ በመሆኑ ለዚህ ሀገራዊ ፕሮጀክት ኢንስቲትዩቱ ያለዉን ሚና አጉልቶ  ማስተዋወቅ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ ኢንስቲትዩቱ የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን አስተዳደሩ ከኢንስቲትዩቱ የቀረቡ የድጋፍ ጥያቄዎች ላይ በቀጣይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰሩባቸዉም አብራርተዋል፡፡

ብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት በምርምር የተደገፉ ለተለያዩ የእንስሳት በሽታዎች ዓለም አቀፍ ደረጃቸዉን የጠበቁ 23 ዓይነት ክትባቶችን የማምረት፣የእንስሳት መድኃኒቶችን ማቀነባበርና ፣ለምርምርና ለእንስሳት በሽታ መመርመሪያ የሚያገለግሉ ባዮሎጂካሎችንና ሪኤጀንቶችን በማምረት ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገር ገበያ አቅርቦ በመሸጥ ትርፍና ትርፋማነትን የማሳደግ ዓላማን ይዞ የተቋቋመ የመንግሥት የልማት ድርጅት ሲሆን በዚህ በጀት ዓመት 60ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ለማክበር በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡

 

                                    የኢንስቲትዩቱ ህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *