የሚኒስትሮች ምክር ቤት የሀገር ውስጥ የክትባት ምርትን አቅም ለመፍጠር የሚያስችሉ ሁለት ደንቦችን አጸደቀ

የሀገር ውስጥ ክትባት የማምረት አቅምን መገንባት አንዱ የመንግስት ትኩረት ሲሆን ይህንን ለመሳካት ዘርፈ ብዙ ስራዎች የጤና ሚኒስቴር ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ ይገኛል፡፡

በዛሬው እለትም ይህንን ጥረት አንድ ምእራፍ የሚያሻግር የሰው ክትባት ለማምረት የሚቋቋመውን የሺልድቫክስ (ShieldVax) ኢንተርፕራይዝን እና ነባሩን የብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት (NVI) በማካተት እንዲቋቋም የቀረበውን የኢትዮ-ባዮፋርማ ግሩፕን የማቋቋሚያ ደንቦች በዛሬው ዕለት የሚንስትሮች ምክር ቤት አጽድቋል። ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ አያሌ የሆኑ በሽታዎችን በጋራ ለመቆጣጠር ታሳቢ በማድረግና ክትባት በማምረት ለሀገር ዉስጥና ለውጭ ሀገር በማቅረብ የ60 ዓመት ልምድ ያለውን የብሔራዊ እንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩትን ጨምሮ የተቋቋመው ግሩፑ ለሰውም ሆነ ለእንስሳት ጤና አስፈላጊ የሆኑ ለህክምና አገልግሎት የሚውሉ ምርቶችን (ክትባት፣ ፋርማሲዩቲካል፣ የህክምና መገልገያዎችን እና መመርመሪያዎችን) የሚያመርትና ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገራት ገበያ የሚያቀርብ ይሆናል።

ደንቦቹ መጽደቃቸው እነዚህ አስፈላጊ ምርቶች ዘላቂ እና ጥራታቸው የተረጋገጠ እንዲሆኑ በማድረግ እና ተደራሽነታቸውን በማሻሻል በራስ አቅም ሀገራዊ የማህበረሰብ ጤናን ለመጠበቅ ትልቅ ምዕራፍ ነው። ይህም የሀገሪቱን የአደጋ ጊዜ ዝግጁነት ለማረጋገጥ እና ጠንካራ የጤና አጠባበቅ ስርዓት ለመፍጠር መሰረትን ይጥላል። በተጨማሪም የግሩፑ መመስረት የማኑፋክቸሪንግ ቴክኖሎጂ እውቀትንና ክህሎትን ሽግግር በሰውና በእንስሳት ጤና ለማሳደግ እና ለኢኮኖሚውም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ከመተካትና የኤክስፖርት አቅምን ከማጠናከር ስትራቴጂያችን ጋር የተጣጣመ እና በዘርፉ የስራ ዕድልን የሚፈጥር ነው።

የዚህ ግሩፕ እና ኢንተርፕራይዝ ምስረታ ወቅታዊ እና የአፍሪካ ህብረትም በ2040 ለአፍሪካ ከሚያስፈልጋት 60%ቱን ክትባት ለማምረት ካለው እቅድ ጋር የተመጋገበ ሲሆን በእንስሳት ጤና ዘርፉም የአብድ ውሻ በሽታንና የትናንሽ አመንዣጊ የደስታ በሽታን ከአለም ለማጥፋት አየተደረገ ያለውን ዘመቻ ለመደገፍ አቅም ለመፍጠር የሚረዳ ነው።