ኢንስቲትዩቱ ባለፉት አስር ወራት ወደ ተለያዩ የአፍሪካ አገራት ከላከው የእንስሳት ክትባት 800 ሺህ ዶላር ገቢ አገኘ

ብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት ባለፉት አስር ወራት ወደ ተለያዩ የአፍሪካ አገራት ከላከው የእንስሳት ክትባት 800 ሺህ ዶላር ገቢ አገኘ

ብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት በአሁኑ ጊዜ 23 ዓይነት የእንስሳት በሽታ መከላከያ ክትባቶችን እያመረተ ይገኛል፡፡

በዚህም የሚያመርታቸውን ክትባቶች ወደ ጎረቤትና ሌሎች የአፍሪካ አገራት በመላክ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ማግኘት ችሏል፡፡

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬከተር ዶክተር ታከለ አባይነህ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኢንስቲትዩቱ በእንስሳት ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ድጋፍ የሚያደርግ ተቋም መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህም የአገር ውስጥ የእንስሳት ክትባት ፍላጎትን ሙሉ ለሙሉ በመሸፈን ለክትባት ግዥይወጣ የነበረን የውጭ ምንዛሪ ማስቀረቱንም ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም እንስሳት በሽታ መመርመሪያ ኪቶችን እና የእንስሳት መድሃኒቶችን በማምረት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ የአገር ውስጥ ፍላጎትን ከመሸፈን ባለፈ ባለፉት አስር ወራት ወደ ተለያዩ የአፍሪካ አገራት ከላከው 21 ነጥብ 29 ሚሊዮን ዶዝ ክትባት 800 ሺህ ዶላር ገቢ ማግኘት መቻሉንም ነው ዋና ዳይሬክተሩ የገለጹት፡፡

ከዚህ ባሻገር የተለያዩ የአፍሪካ አገራት የ1 ሚሊዮን ዶላር የእንስሳት ክትባት በመጪዎቹ አራት ወራት እንዲቀርብላቸው ጥያቄ ማቅረባቸውን ገልጸው፤ ኢንስቲትዩቱ ይህንን ለማሟላት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢንስትቲዩቱ በተለይ በአፍሪካ ያለውን ፍላጎት ለማሟላት ተጨማሪ ዘመናዊ የማምረቻ መሳሪያዎች እንደሚያስፈልጉት የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ለመሳሪያ ግዥ የሚሆን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ደግሞ በዚህ ረገድ ፈተና መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም መንግስት ኢንስትቲዩቱን በግብዓት እንዲሟላ ድጋፍ በማድረግ ኢትዮጵያ በተለይ በአፍሪካ ያለውን የገበያ እድል እንድትጠቀም  ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይገባል  ነው ያሉት፡፡

የብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት ከተመሰረተ 58 ዓመት ያስቆጠረ ሲሆን፤ አሁን ላይ በዓመት 350 ሚሊዮን ዶዝ ክትባት እያመረተ ይገኛል፡፡

                                                 ሰኔ 13/2014/ኢዜአ/ እንደዘገበዉ