የኢፌድሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብት ልማት ስምሪት ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ኢንስቲትዩቱን ጎበኙ
የኢፌድሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብት ልማት ስምሪት ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ብሔራዊ የእንሰሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩትን ጎበኙ፡፡ በዚህ ጉብኝት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች፣ የባዮና ኢመርጂንግ ኢንስቲትዩት እና የክልል የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ተቋማት የስራ ሀላፊዎች፤ የዩኒቨርስቲ ምሁራን፤ የምርምር ተቋማትና የዘርፉ ተዋናዮች ተሳትፈውበታል። ልዑካን ቡድኑ የብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዪትን የ60 አመታት ስኬታማ ጉዞ ገለፃ ተደርጎላቸዋል፡፡


የኢንስቲትዩቱ የምርምርና ስርፀት ዳይሬክተርና የዋና ዳይሬክተር ተወካይ ዶ/ር ምርትነህ አካሉ ኢንስቲትዩቱ ከምስረታው ጀምሮ የነበረውን የስኬት ጉዞ፤ የኢንስቲትዩቱን ዋና ዋና ተግባራት፤ የክትባትና የመድሃኒት ምርትና ስርጭትን፤ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና ከባዮና ኢመርጂንግ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ስለሚሰሩ የምርምርና ልማት ስራዎች፤ ከሌሎች የምርምር አጋሮች ጋር የተሰሩ የምርምር ስራዎችና ውጤታቸው፤ የማህበረሰብ አቀፍ አበርክቶዎች፤ ኢንስቲትዩቱን እያጋጠሙ ስላሉ ተግዳሮቶችና የወደፊት የማስፋፊያ ስራዎች፤ እንዲሁም በአጠቃላይ ኢንስቲትዩቱ ለሃገር እያበረከተ ያለውን ፋይዳ ለቋሚ ኮሚቴዉና ለክብር እንግዶች ገለፃ አድርገዋል፡፡
የኢፌድሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብት ልማት ስምሪት ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ዶ/ር ነገሪ ሌኔጮ የአብዛኛውን የአርሶ አደርና የከተማ ማህበረሰብ ህይወት እንዲቀየር በሁሉም ዘርፎች መፍትሔ የሚያመጡ ጥናትና ምርምሮች ወሳኝ በመሆናቸዉ ኢንስቲትዩቱ የግብርናዉን ዘርፍ የሚደግፍ ለሀገሪቱ የጀርባ አጥንት የሆነ ተቋም እንደሆነ ከጉብኝቱ መረዳት እንደቻሉ ገልጸዋል። ኢንስቲትዩቱ በምርምር የሚያበለፅጋቸውን የእንስሳት በሽታ መከላከያ ክትባቶችን ወደ ገበያው በማስገባት ለተጠቃሚው ማድረስ መቻሉ የኢንስቲትዩቱን የመፈፀም አቅም የሚያሳይ ነው፡፡ በተጨማሪም በኢንስቲትዩቱ እና በባዮና ኢመርጂንግ የምርምር አቅም የለሙና በምርምር ላይ ያሉ የእንስሳት የበሽታ መከላከያ ክትባቶች መኖራቸው ይበል የሚያሰኝና በጋራ የሚለሙ የምርምር ውጤቶች ማስፋት የአገሪቱን የእንስሳት ምርትና ምርታማነት በመሳደግና በመደገፍ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዳላቸው አፅንዖት ሰተዋል፡፡ የጋራ የምርምር ጅምሮች አሁን ባለው ደረጃ ብቻ ተወስነው መቅረት እንደሌለባቸውና ይልቁንም አገሪቱ በብዙ የውጭ ምንዛሪ የምታስገባቸውን የኢንደስትሪ ግብአቶች በጋራ ማልማትና መስራት እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል፡፡ ኢንስቲትዩቱ እየተጠቀመባቸው ያሉ የቴክኖሎጂ ስራዎች ጥሩ ቢሆኑም ከደንበኞች ጋር የማስተሳሰር ስራ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚንስትር ዲኤታ ዶ/ር ባይሳ ባዳዳ በዓለም ላይ በሳይንስ፣ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ላይ መሰረተ ልማትና ምቹ ስነምህዳር የገነቡ ሀገራት በኢኮኖሚው ግንባር ቀደም እንዲሆኑ እንደዚህ አይነት ተቋማት ሚናቸዉ የጎላ ነዉ ብለዋል። ኢንስቲትዩቱ ያለው አቅምና ለአገር እያበረከተ ያለውን ስራ መደገፍ እንደሚገባ በማስረዳት፤ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በቀጣይ ኢንሰቲትዩቱ ለሚሰራቸው የምርምር ስራዎች ድጋፍ እንደሚደረግ ገልፀዋል፡፡


በመጨረሻም ተሳታፊዎች ብሔራዊ የእንሰሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት የስራና የምርምር ውጤቶች ላይ የተዘጋጀውን አውደ ርዕይ ጎብኝተዋል።
የኢንስቲትዩቱ ኮሙኒኬሽን
ሰኔ /2017 ዓ.ም
