የኢፌድሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ኢንስቲትዩቱን ጎበኙ


ታህሳስ 27፣ 2018 ዓ.ም ፤ የኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት ባደረጉት የመስክ ምልከታ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ መለሰ መና ፣ የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ ኮሬ እና የኮሚቴዉ አባላት ተገኝተዋል።
አላማዉም ኢንስቲትዩቱ የተቋቋመበትን ዓላማ ከማሳካት አንጻር ከክትባት እና መድሃኒት ምርት አኳያ አሁን ያለበትን የአፈፃፀም ደረጃ በመገምገም የተገኙ ጠንካራና ደካማ ጎን እንዲሁም ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን በመለየት ግብረ መልስ በመስጠት የተቋሙ አገልግሎት ፈጣን ፣ቀልጣፋ ለማድረግ መሆኑን የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ መለሰ መና ገልጸዋል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ታከለ አባይነህ ስለ ክትባትና መድኃኒት አመራረት ዘርፍ የግንዛቤ ማስጨበጫና የፖሊሲ ድጋፍ የሚፈልጉ ጉዳዮቸን እንዲሁም፣ ስለተቋሙ አጠቃላይ እንቅስቃሴና ያለበትን የአፈጻጸም ደረጃ ለቋሚ ኮሚቴዉ አብራርተዋል፡፡


ተቋሙ በቀጣይ አሁን እየሰራ ካለበት ቴክኖሎጂ ወደ ተሻለ ለማሸጋገርና አለም አቀፍ ተወዳዳሪ ሆኖ እንዲቀጥል መልካም የአመራረት ዘዴን መስፈርት የሚያሟላ ዘመናዊ የእንሰሳት ክትባት ማምረቻ ላብራቶሪ እንዲሁም ሌሎች ወሳኝ የማምረቻ ማሽኖችን ለመተካት የአዋጪነት ጥናት ለማከናወን በሂደት ላይ መሆኑን ገልፀዉ ኢንስቲትዩቱ ከሚያገኘው ትርፍና የውጭ ምንዛሪ ባሻገር ለእንስሳት ሀብት ልማት ዘረፉ የሚያበረክተዉ አስተዋጾ በእጅጉ የጎላና ቁልፍ ሚና ያለው በመሆኑ አመራረቱንና የምርቶቹን ግብይት ለማሳለጥና በፖሊሲ ሊደገፍ ይገባል ብለዋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ የግብይትና ሽያጭ ዳይሬክተር አቶ መስፍን ታደሰ ከክትባት እና መድሃኒት ግብይት ጋር በተያያዘ ያለዉን ነባራዊ ሁኔታ አቅርበዋል።
ቋሚ ኮሚቴዉ ከሰራተኛዉ ጋር በምርት ስራዎች፣ በሰዉ ሃብት አስተዳደር እና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ዉይይት አካሂዶ አመራሩና ሰራተኛዉ የኢንስቲትዩቱን ራዕይ ለማሳካት በቅርበት ለችግሮች መፍትሄ በማስቀመጥ የኢንስቲትዩቱን ትርፋማነት ሊያስቀጥል እንደሚገባ የቀጣይ አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡

